Anointed Jesus international church

ወንጌል ያሸንፋል

በሰው እና በእግዚአብሔር መሃል አንድ ኢየሱስ ብቻ!

አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤"1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2:5)

             መካከለኛ የሆነው ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ የሆነው አንድ ጌታ እርሱ ኢየሱስ ብቻ ነው። የሰው ዘር መካከለኛ እንዳይሆን  ፍጡር ሁሉ ሃጥያተኛ ነው ከዚያም ደግሞ መካከለኛነቱ ለፍጡር እንጂ ለፈጣሪ አይሆንም። ምክንያቱም መካከለኛ መሆንን ሚችለው ሰውም አምላክም የሆነ ብቻ ነው። ፍጡር ደግሞ ፍጡር ብቻ ነው ። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው ያውም የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ ነው እርሱ ሰው የሆነ አምላክ እንዲሁም አምላክ የሆነ ሰው በመሆኑ ነው። አባቶች በምስጢረ ስጋዌ ሲያስተምሩ ዘእንበለ ውላጤ ዘእንበለ ትድምርት ማለትም ያለ መለወጥ ያለ መጨመር ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ ነው። ስለዚህም ኢየሱስ በአምላክነቱ እግዚአብሔርን በሰውነቱ ደግሞ ሰውን ሁሉ ወክሎ በሰማይ ያለ መካከለኛ ነው። ሰውም አምላክም ያልሆነ መካከለኛ ሊሆን መካከለኛም ሊባል  አይችልምና። 

                       " ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።"1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2:1 ። ከአብ ዘንድ የሆነ ማለት አምላክ የሆነ ማለት ነው ምክንያቱም ማንም ፍጡር በመፅሃፍ ቅዱስ ከአብ ዘንድ ተብሎ አያውቅም ። ከዚያም ደግሞ ጻድቅ የሆነ ሲል ደግሞ ሰው መሆኑን እያሳየን ነው።  እናስተውል ሰው ስንል ግን  ፍጡር ማለት አይደለም ኢየሱስ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ ነው። ስለዚህ መካከለኛ ሆኖ ከአብ ዘንድ ለእኛ የተሰጠን እግዚአብሔርን የወከለ እርሱ ብቻ ነው ደግሞ እርሱም ሰው የሆነ እግዚአብሔር ነው። ወደ እግዚአብሔርም መቅረብም ሆነ መሄድ ምንችለው በእርሱ ብቻ ነው። " ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።"ዮሐንስ ወንጌል 14:6 

              እግዚአብሔር አብ ሊያድነን የወደደውም የፈቀደውም በልጁ በኩል ብቻ ነው ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰውን የታደገው እና ያዳነው በልጁ ደም መፍሰስ እና የመስቀል ሞት ነው። " ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።" ዕብራውያን 7:25 በእርሱ ህያው እና ዘላለማዊ በሆነው  በኩል ካልሆነ መዳን በሌላ በኩል የለም። 

ከእርሱ ደም ውጭ ስለእኛ የፈሰሰልን ሌላ መስዋዕት የለምና እግዚአብሔርም ከልጁ መስዋዕት ውጭ ሌላ ያስደሰተው ቅዱስ መስዋዕት ስለሌለ በልጁ ብቻ ነው እኛን ያዳነን ። አሜን ስሙ ይክበር ።  

 

      እግዚአብሔር አብ ፀሎት ልመና እና ምስጋናችንንም በልጁ ስም ነው ሚቀበለን እርሱም ጌታችን ስለ ስሙ ክብር በራሱ ስም ነው ልመናችንን ሚቀበለን። ምናደርገውን ሁሉ በእርሱ በልጁ ስም ብቻ እንድናደርግ ነው መፅሃፍ ያዘዘን።ዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 14) 13፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። 14 ፤ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ። " በዚያን ቀንም ከእኔ አንዳች አትለምኑም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል።"ዮሐንስ ወንጌል 16:23

" እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት። "ቆላስይስ ሰዎች 3:17

               ስለዚህ በሰው እና በእግዚአብሔር መሃል ያለው መካከለኛ አንድ ነው ።መፅሃፍ ሌላ አለ ቢለን እንቀበል ነበር ነገር ግን እናስተውል እንዲህ  አላለንም ቅዱሱ የእግዚአብሔር ቃል። 

         ሃይማኖተ አበው ገጽ 330 ቁጥር 68 እንዲህ ይለናል ወውዕቱ መዋኤ ኲሉ ኀጢአት ኮነነ ሊቀ ካህናት በትስብእቱ ወከመ ላእከ ሦአ ሥጋሁ ንፁህ ለእግዚአብሔር አብ በእንቲአነ። ትርጉም፦ሃጢአትን ሁሉ የሚያጠፋ እርሱ ነው በመሆኑ አስታራቂ ሆነ እንደ አገልጋይም ሆኖ ንፁህ ሥጋውን ለእግዚአብሔር አብ ስለ እኛ ሰዋ። 

            ስለዚህም የሰውንም የእግዚአብሔርንም ማንነት ወክሎ መካከለኛ ሊሆን ሚችል ብቃት ያለው ማንም የለም ። ሰውም መለኮትም የሆነ የሁለቱንም ማንነት ሊሆን የሚችል መካከለኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። 

               

          2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕ. 5) 18፤ ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ 19 ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።20፤ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። እዚህ ጋር ስናይ እግዚአብሔር በክርስቶስ ከራሱ ጋር አስታርቆናል ክርስቶስም በማስታረቅ አገልግሎናልና ነው የማስታረቅ አገልግሎት ከሰጠን ብሎ ማለቱ ለዚህ ነው ይህም ስላስታረቀን ነው። ከዚያም አልፎ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ ይላል እናስተውል ሃዋርያው ያለው የማስታረቅ ቃል አኖረ እንጂ የማስታረቅ አገልግሎት አኖረ አላለም ምክንያቱም የማስታረቅ አገልግሎት በእኛ አኖረ ካለ ፍፁም ነን ሃጥያት የለብንም ስለዚህ ከኢየሱስ ደም ጋር የራሳችንን ማንነት ለስርየት ለማስታረቅ ይዘን የመቅረብ ብቃት አለን ሊል ነዋ? በጭራሽ አላለም እናስተውል የማስታረቅ ቃል እና የማስታረቅ አገልግሎት ልዩነት አላቸው። 

    የማስታረቅ አገልግሎት ለጌታችን ለኢየሱስ ብቻ የተገባው ነው ምክንያቱም ፍፁም ፃድቅ ሰው እና አምላክ እርሱ ብቻ ስለሆነ። በእኛ ግን የማስታረቅን ቃል አኑሯል ያኖረው እኛ ለእግዚአብሔር መልዕክተኞች ሆነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እያልን ቃሉን እንድናውጅ ነው ይህም የአዋጅ ቃል ይህ ነው። በህይወት ዘመናችን ሆነን ልናደርገው ምንችለው ሂደት ብቻ ነው።

                   1ኛ የዮሐንስ መልእክት ምዕ. 1 ።8፤ ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።9 በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።ንስሃ ግቡ ከአግዚአብሔር ጋር በልጁ በኢየሱስ ደም ታረቁ የልጁ የኢየሱስ ደም ከሃጥያት ሁሉ ያነፃል እያልን መልዕክተኞች እንሆን ዘንድ ነው። ይህን ያለው ሃዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን በእኛ በኩል እንዲያገኛቸው ማለት ነው ይህም ማለት በስብከታችን በምስክርነታችን በምግባራችን ምክንያቱም የማስታረቅን ቃል በእኛ አኑሯላ። እዚህ ጋር ከእግዚአብሔር ወደ ሰዎች ስለ መሄድ እንጂ ከሰዎች ወደ እግዚአብሔር ስለ መላላክ አይደለም። በእርግጥ በህይወት ዘመን ሰው ስለ ሰው ሊፀልይ እና ሊለምን ይችላል ። ስለዚህ ሰዎች ይህን ቃል ካልሰሙ እንዴት አርገው ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ።  " እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?"ወደ ሮሜ ሰዎች 10:14።

          ስለዚህ እኛ ለሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እያልን እንማልዳለን።ሰው ደግሞ ከሰው ጋር መገናኘት ሚችለው በህይወት በምድር ላይ እስካለ ብቻ ነው። ከሞተ በኋላ ከሰው ጋር በምንም ሊገናኝ አይችልም። ወይም ከሰው ጋር ለመገናኘት እንደ እግዚአብሔር ምሉዕ በኩለሄ ማለትም በሁሉ ስፍራ ያለ ሊሆን ይገባዋል። ሰው ደግሞ በየትኛውም የክርስትና ህይወት እና በመፅሃፍ ቅዱሳችንም ምሉዕ በኩለሄ ሆኖ አያውቅም። ከሞትም ተነስቶ ለመልዕክተኛ የሆነ እና ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ያለ ማንም የለም።

            አብርሃም እንኳን ለዚያ ለባለ ጠጋው ሰው ምንድን ነው ያለው። ባለጠጋው ሰውዬ አልአዛርን በእቅፍህ አለ ስደድልኝ ሲለው ሙሴን እና ነቢያቱ አሉላቸው እነርሱን ይስሙ ነው ያለው።  በህይወት ያሉትን ካልሰሙ ከሙታን ተነስተውም ቢሄዱላቸው አይሰሙም ነው ያለው። የሉቃስ ወንጌል ምዕ. 16÷ 28፤ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ።29፤ አብርሃም ግን። ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው።30፤ እርሱም። አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ።31፤ ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።

             ስለዚህ ለማንኛውም ሰው የተሰጠው ቅዱሳንም ይሁን ሰማዕታት ፃድቃን በምድር ላይ እያሉ መልዕክተኛ የመሆን ይሄውም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እያሉ ወንጌልን የመመስከር እንጂ ከሞቱ በኋላ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የማስታረቅ ስልጣን ለማንም ፍጡር አልተሰጠም። ምክንያቱም ሰውን እና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ ስለ እዚያ ሰው ሃጢአት ማስተሰርያን ሊያቀርቡ ይገባል ይህን እንዳያቀርቡ ደግሞ ከሰው ወገን ፍፁም የሆነ ስለሌለ ደማቸው ካሳ ሊሆን አይችልም ። ሞትንም አሸንፈው ሊያርጉ አይችሉም ምክንያቱም ሞትን ለማሸነፍ 100% ፅድቅ ያስፈልጋል ይህን ደግሞ ማንም በራሱ አልቻለም አይችልም። ስለዚህ ለሰው ልጆች የማስታረቅ አገልግሎት የተሰጣቸው በምድር ላይ እያሉ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለው ወንጌልን ቃሉን መናገር ነው የተሰጣቸው ። በምድር ሲማልዱም ስለ እኔ ብለህ ይቅር በል ማለትን አይችሉም ምክንያቱም እግዚአብሔር ስለ ልጁ ደም ብቻ ነው ይቅር የሚለው። ንፁህ መስዋዕት የኢየሱስ ብቻ ነውና። ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ የበጉን ዙፋን ከበው ይገባሃል ቅዱስ ማለት ነው ስራቸው።ዮሐንስ ራእይ ምዕ. 5) 11፤ አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር12፤ በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።

            " መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።"

(የሐዋርያት ሥራ 4:12)